| Wednesday, 13 August 2008 | |
|
አባ ኃይለ ሚካኤል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የጊዜ ቀጠሮ መሠጠቱ ተሰማ አባ ኃይለ ሚካኤል ታደሰ በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ የመንበረ ቅዱስ ሚካኤልና ገብርኤል ደብሮች አስተዳዳሪ ከሐምሌ 23 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም አንሥቶ በግልፅ ባልታወቀ ምክንያት በእሥር ላይ የቆዩ ሲሆን ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ተከልክለው ነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በሌሉበት ለነሐሴ 7 ቀን 2000 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ መሰጠቱ ተሰማ፡፡ አባ ኃይለ ሚካኤል ወደ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የተከለከሉት በአካባቢው ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ የሚሰጥባቸውን ብይን ለመስማት ተሰብስቦ ስለታየ የፀጥታ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ተገምቶ እንደነበር ታውቋል፡፡የሕግ ባለሙያዎችና የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች ግን ለፀጥታ ሥጋት ጥበቃን ማጥበቅ ሳለ አባ ኃይለ ሚካኤል ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ መከልከላቸው ተገቢ እንዳልነበር ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ ቀደም ሲል አባ ኃይለ ሚካኤል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ የተያዘላቸው ለሐምሌ 3ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም ሲሆን በዚሁ ዕለትም በችሎቱ አካባቢ ሕዝብ በብዛት ተሰብስቦ በመታየቱ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባሁኑ ወቅት አባ ኃይለ ሚካኤል በመታሠራቸው በደብሮቹ ውስጥ በሚገኙ ፅላቶችና በሌሎች ንዋየ ቅዱሳት ላይ ወንጀል እንዳይፈፀም ምዕምናኑ ደብሮቹን እየጠበቁ መሆኑንም የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች አስታውቀዋል፡፡ በሌላም በኩል እንደ አባ ኃይለ ሚካኤል ሁሉ በግልፅ ተለይቶ ባልታወቀ ጉዳይ ከሐምሌ 29 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም አንስቶ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ፖሊስ ጣቢያ ታሥረው የቆዩት 1. አቶ ዘውዱ ጥላሁን 2. አቶ ዮሐንስ ፋንታ እና 3. ወይዘሮ ጦቢያ ወልደ ጊዮርጊስ ነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በዋስ መለቀቃቸውን ከአርባ ምንጭ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ |