ድረገጾቻችን በብሄራዊ ቋንቋችን  ማዘጋጀት የማንነታችን መግለጫ ነው!በላቲን መፃፍ  የራስን ንቆ  የበታችነትን መቀበል እንጅ ሊቅነት አይደለም!
                    ዜና                                                          ታሪክህን ዕወቅ

 

የቅንጅት አባላት እርዳታ እንደ ተከለከሉ ታወቀ    
Wednesday, 13 August 2008

     በአራት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል የሚመራው  የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት በሥርዓተ-አገዛዙ ሰብዓዊ እርዳታዎች እንዳይሰጣቸው የተከለከሉ መሆኑን ሰሞኑን የየዞኑ የፓርቲው ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በሰጡት መግለጫ ታወቀ፡፡

      በዚህም መሠረት በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ሃያ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ በተራበው ሕዝብ ስም ከተላከው የምግብ ዕህል እርዳታ ለማንኛውም በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ለሚመራው ፓርቲ አባልና ለቤተሰቡ የማይሰጥ ሲሆን የፓርቲው አባላት በምግብ የሥራ መርሐ-ግብር የመሳተፍ መብታቸውም የተገፈፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

     አባላቱ በስሕተት እርዳታ አግኝተው ቢገኙ እንኳን ወይም በሥራ መርሐ-ግብር መሣተፋቸው ቢታወቅ ወዲያው ያገኙትን ጥቅማ ጥቅም ተቀምተው እንዲሁም በአገዛዙ አካላትና በካድሬዎች ተደብድበው እንደሚባረሩ ታውቋል፡፡

     በተመሣሣይ መልኩ በወላይታ፤ በጌዴኦና በጎፋ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ሰላሣ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል የሚመራው የቀድሞ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት በተራበው ሕዝብ ስም ከውጭ ሀገር ከሚላከው የምግብ እርዳታ ምንም የማይሰጣቸው ሲሆን የፓርቲው አባል ቤተሰብ አባላት የሆኑ ታማሚ ሕፃናት እንኳን በሕፃናት ስም የመጡ አልሚ ምግቦችን እንዳያገኙ በአገዛዝ አካላት የተከለከሉ መሆናቸውን ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

     በሁሉም ዞኖች የአገዛዝ አካላት "ቅንጅት ይመግባችሁ! የእናንተ መንግሥት ቅንጅት አይደል?" እያሉ በፓርቲው አባላት ቤተሰቦች ላይ የሚያላግጡ ሲሆን ረኃብተኞቹ በሕዝብ ስም ከመጣው እርዳታ የማግኘት መብት እንዳላቸው ጠቅሰው ለበላይ አካላት ቢያመለክቱም አዎንታዊ መልስ እንዳልተጣቸው ታውቋል፡፡

          


ጽሁፍና አስተያየት